ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 4:29-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ከተቀመጡበትም ተነሥተው ከከተማው አስወጡት፤ ቊልቊል ሊጥሉትም ከተማቸው ወደ ተሠራች በት ኰረብታ አፋፍ ወሰዱት፤

30. እርሱ ግን በመካከላቸው ሰንጥቆ ሄደ።

31. ከዚያም በገሊላ አውራጃ ወደምትገኘው ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም በሰንበት ዕለት ሕዝቡን ያስተምር ጀመር፤

32. የሚናገረው በሥልጣን ስለ ነበር በትምህርቱ ተደነቁ።

33. በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ እርሱም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኾ፣

34. “ወዮ! የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ምን የሚያገናኘን ጉዳይ አለ? የመጣኸው ልታጠፋን ነውን? አንተ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” አለው።

35. ኢየሱስም፣ “ጸጥ ብለህ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያደርስበት ለቆት ወጣ።

36. ሰዎቹም ሁሉ ተገረሙ፤ እርስ በእርሳቸውም፣ “ለመሆኑ ይህ ትምህርት ምንድን ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዛል፤ እነርሱምኮ ይወጣሉ” ተባባሉ።

37. የእርሱም ዝና በአካባቢው ወዳለው ስፍራ ሁሉ ወጣ።

38. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከምኵራብ ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት ኀይለኛ ትኵሳት ይዞአት ታማ ነበር፤ እንዲፈውሳትም ስለ እርሷ ለመኑት።

39. እርሱም ወደ ተኛችበት ጠጋ ብሎ በማጐንበስ ትኵሳቱን ገሠጸው፤ ትኵሳቱም ለቀቃትና ወዲያው ተነሥታ አስተናገደቻቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 4