ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 4:21-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. እርሱም፣ “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ይላቸው ጀመር።

22. ሁሉም ስለ እርሱ በበጎ ይናገሩ ነበር፤ ደግሞም ከአንደበቱ በሚወጣ የጸጋ ቃል እየተገረሙ፣ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።

23. እርሱም፣ “ ‘ባለ መድኀኒት ሆይ፤ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም ስታደርግ የሰማነውን ነገር እዚህ በራስህ ከተማ ደግሞ አድርግ’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ ጥርጥር የለውም” አላቸው።

24. ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም።

25. ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ተዘግቶ ጽኑ ራብ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በነበረበት በኤልያስ ዘመን፣ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ነበሩ፤

26. ኤልያስ ከእነዚህ መካከል ወደ አንዷም አልተላከም፤ ነገር ግን በሲዶና አገር በሰራፕታ ወደ ነበረችው መበለት ተላከ።

27. በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነዚያ መካካል ማንም አልነጻም።”

28. በምኵራብ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በቍጣ ገነፈሉ፤

29. ከተቀመጡበትም ተነሥተው ከከተማው አስወጡት፤ ቊልቊል ሊጥሉትም ከተማቸው ወደ ተሠራች በት ኰረብታ አፋፍ ወሰዱት፤

30. እርሱ ግን በመካከላቸው ሰንጥቆ ሄደ።

31. ከዚያም በገሊላ አውራጃ ወደምትገኘው ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም በሰንበት ዕለት ሕዝቡን ያስተምር ጀመር፤

32. የሚናገረው በሥልጣን ስለ ነበር በትምህርቱ ተደነቁ።

33. በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ እርሱም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኾ፣

34. “ወዮ! የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ምን የሚያገናኘን ጉዳይ አለ? የመጣኸው ልታጠፋን ነውን? አንተ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” አለው።

35. ኢየሱስም፣ “ጸጥ ብለህ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያደርስበት ለቆት ወጣ።

36. ሰዎቹም ሁሉ ተገረሙ፤ እርስ በእርሳቸውም፣ “ለመሆኑ ይህ ትምህርት ምንድን ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዛል፤ እነርሱምኮ ይወጣሉ” ተባባሉ።

37. የእርሱም ዝና በአካባቢው ወዳለው ስፍራ ሁሉ ወጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 4