ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 24:2-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ድንጋዩም ከመቃብሩ ደጃፍ ተንከባሎ አገኙት፤

3. ወደ ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን ሥጋ አላገኙም።

4. በሁኔታው ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ እነሆ፤ እጅግ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ።

5. ሴቶቹም ከመፍራታቸው የተነሣ ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፣ ሰዎቹ እንዲህ አሏቸው፤ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ?

6. እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤

7. ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና።”

8. ሴቶቹም በዚህ ጊዜ ቃሉን አስታወሱ።

9. ሴቶቹ ከመቃብሩ ስፍራ ተመልሰው ይህን ሁሉ ነገር ለዐሥራ አንዱና ለተቀሩት ሁሉ ነገሯቸው።

10. ይህን ለሐዋርያት የነገሯቸውም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐና፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ።

11. እነርሱ ግን ሴቶቹ የተናገሩት ቃል መቀባዠር ስለ መሰላቸው አላመኗቸውም።

12. ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያ ደርሶም ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ በፍታው እንዳለ ለብቻው ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተገረመ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

13. በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 24