ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ጢሞቴዎስ 4:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።

6. እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።

7. መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።

8. ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።

9. በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤

10. ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዶአልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤

11. ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና።

12. ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ።

13. ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖስ፣ ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ።

14. አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጒዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል።

15. መልእክታችንን እጅግ ተቃውሞአልና፣ አንተም ከእርሱ ተጠንቀቅ።

16. በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ጢሞቴዎስ 4