ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ጢሞቴዎስ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤

2. ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።

3. ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።

4. እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።

5. አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።

6. እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።

7. መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።

8. ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።

የጳውሎስ ማሳሰቢያ

9. በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤

10. ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዶአልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤

11. ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና።

12. ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ።

13. ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖስ፣ ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ።

14. አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጒዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል።

15. መልእክታችንን እጅግ ተቃውሞአልና፣ አንተም ከእርሱ ተጠንቀቅ።

16. በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው።

17. ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳም መንጋጋ አዳነኝ።

18. ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

የስንብት ሰላምታ

19. ለጵርስቅላና ለአቂላ፣ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ።

20. ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቶአል፤ ጥሮፊሞስም ስለ ታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ።

21. ከክረምት በፊት እዚህ ለመምጣት የተቻለህን አድርግ። ኤውግሎስና ጱዴስ እንዲሁም ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

22. ጌታ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።