ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 5:11-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እንጥራለን። የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠ ነው፤ ደግሞም በኅሊናችሁ ዘንድ ግልጽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

12. ይህን የምለው ራሳችንን በእናንተ ፊት እንደ ገና ለማመስገን ሳይሆን፣ በእኛ እንድትመኩ ዕድል ልሰጣችሁ ነው፤ ይኸውም በውጭ በሚታየው ለሚመኩት እንጂ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ለማይመኩ መልስ መስጠት እንድትችሉ ነው።

13. ከአእምሮ ውጪ ብንሆን ለእግዚአብሔር ብለን ነው፤ ባለ አእምሮም ብንሆን ለእናንተ ነው።

14. የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል።

15. በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።

16. ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በውጫዊ ነገር አንመዝንም፤ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን በዚህ መልክ መዝነነው ነበር፤ ከእንግዲህ ግን እንደዚህ አናደርግም።

17. ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ አዲስ ሆኖአል።

18. ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን፤ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤

19. እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር፤ ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን።

20. ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን።

21. እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 5