ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 12:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. እኔ ግን ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ብሰጥ ደስ ይለኛል፤ ታዲያ እኔ የምወዳችሁ ይህን ያህል ከሆነ፣ እናንተ የምትወዱኝ በጥቂቱ ነውን?

16. የሆነው ሆኖ ሸክም አልሆንሁባችሁም፤ ነገር ግን በተንኰልና በዘዴ ያጠመድኋችሁ ሳይመስላችሁ አልቀረ

17. ለመሆኑ ወደ እናንተ በላክኋቸው ሰዎች አማካይነት በአንዱ እንኳ በዘበዝኋችሁን?

18. ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ለመንሁት፤ ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ላክሁት። ቲቶ በዘበዛችሁን? ከእርሱ ጋር በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረምን?

19. እስከ አሁን ድረስ በእናንተ ፊት ራሳችንን ስንከላከል የኖርን ይመስላችኋልን? በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንናገራለን፤ ደግሞም ወዳጆች ሆይ፤ ይህን ሁሉ የምናደርገው እናንተን ለማነጽ ነው።

20. ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባትም በመካከላችሁ ጥል፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ አድመኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜት፣ እብሪትና ሁከት ይኖራል ብዬ እሠጋለሁ።

21. ዳግመኛም ስመጣ አምላኬ በእናንተ ፊት ያዋርደኝ ይሆን ብዬ እፈራለሁ፤ ይኸውም ብዙዎች ከዚህ በፊት ስለሠሩት ኀጢአትና ስለ ፈጸሙትም ርኵሰት፣ ዝሙትና መዳራት ንስሓ ሳይገቡ ቀርተው እንዳላዝን ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 12