ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጳውሎስ ያየው ራእይና የተሰጠው መውጊያ

1. በመመካት የሚገኝ ጥቅም ባይኖርም፣ መመካት ካስፈለገ ከጌታ ወደ ተቀበልሁት ራእይና መገለጥ አመራለሁ።

2. ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው ዐውቃለሁ፤ የተነጠቀው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል።

3. ይህ ሰው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል፤

4. እርሱም ወደ ገነት እንደ ተነጠቀ፣ በዚያም በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችል፣ ሰውም እንዲናገረው ያልተፈቀደለት ነገር ሰማ።

5. እንደዚህ ስላለው ሰው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ከደካማነቴ በስተቀር አልመካም።

6. መመካት ብፈልግ እንኳ እንደ ሞኝ መቈጠር የለብኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው። ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው በላይ እንዳይገምተኝ ከመመካት እቈጠባለሁ።

7. ከዚህ ታላቅ መገለጥ የተነሣ እንዳልታ በይ የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ።

8. ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት፤

9. እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።

10. ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረው ጭንቀት

11. በመመካቴ ሞኝ ሆኛለሁ፤ ለዚህም ያበቃችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ ስለ እኔ መመስከር የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ። ደግሞም እኔ ከምንም የማልቈጠር ብሆንም፣ “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም አላንስም።

12. የእውነተኛ ሐዋርያ ምልክቶች በመካከላችሁ ተደርገዋል፤ እነርሱም በትዕግሥት መጽናት፣ ምልክቶች፣ ድንቅ ነገሮችና ታምራት ናቸው።

13. በእናንተ ላይ ሸክም ካለመሆኔ በቀር፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በምን አነሳችሁ? ይህን በደሌን ይቅር በሉኝ።

14. ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ስመጣ በምንም ነገር ሸክም አልሆንባችሁም፤ እኔ እናንተን እንጂ ከእናንተ ምንም አልፈልግምና፤ ደግሞም ወላጆች ለልጆች ገንዘብ ያከማቻሉ እንጂ ልጆች ለወላጆች አያከማቹም።

15. እኔ ግን ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ብሰጥ ደስ ይለኛል፤ ታዲያ እኔ የምወዳችሁ ይህን ያህል ከሆነ፣ እናንተ የምትወዱኝ በጥቂቱ ነውን?

16. የሆነው ሆኖ ሸክም አልሆንሁባችሁም፤ ነገር ግን በተንኰልና በዘዴ ያጠመድኋችሁ ሳይመስላችሁ አልቀረ

17. ለመሆኑ ወደ እናንተ በላክኋቸው ሰዎች አማካይነት በአንዱ እንኳ በዘበዝኋችሁን?

18. ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ለመንሁት፤ ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ላክሁት። ቲቶ በዘበዛችሁን? ከእርሱ ጋር በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረምን?

19. እስከ አሁን ድረስ በእናንተ ፊት ራሳችንን ስንከላከል የኖርን ይመስላችኋልን? በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንናገራለን፤ ደግሞም ወዳጆች ሆይ፤ ይህን ሁሉ የምናደርገው እናንተን ለማነጽ ነው።

20. ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባትም በመካከላችሁ ጥል፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ አድመኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜት፣ እብሪትና ሁከት ይኖራል ብዬ እሠጋለሁ።

21. ዳግመኛም ስመጣ አምላኬ በእናንተ ፊት ያዋርደኝ ይሆን ብዬ እፈራለሁ፤ ይኸውም ብዙዎች ከዚህ በፊት ስለሠሩት ኀጢአትና ስለ ፈጸሙትም ርኵሰት፣ ዝሙትና መዳራት ንስሓ ሳይገቡ ቀርተው እንዳላዝን ነው።