ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 9:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. መላው እስራኤል አንተን ባለመታዘዝ ሕግህን ተላልፎአል፤ ዘወርም ብሎአል።“በአንተ ላይ ኀጢአትን ስለ ሠራን፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሓላና ርግማን ፈሰሰብን።

12. ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ በማምጣት፣ በእኛና በገዦቻችን ላይ የተነገረውን ቃል ፈጸምህብን፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገውን የሚያህል ከሰማይ በታች ከቶ የለም።

13. በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈው፣ ይህ ሁሉ ጥፋት በእኛ ላይ ደረሰ፤ ሆኖም ከኀጢአታችን በመመለስና እውነትህን በመከተል ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ምሕረትን አልፈለግንም

14. አምላካችን እግዚአብሔር በሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ ነውና፣ በእኛ ላይ እግዚአብሔር ጥፋት ከማምጣት አልተመለሰም፤ እኛም አልታዘዝነውም።

15. “አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በብርቱ እጅ ያወጣህ፣ እስከዚህም ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግህ፣ ጌታ አምላካችን ሆይ፤ እኛ ኀጢአትን ሠርተናል፤ አንተንም በድለናል።

16. ጌታ ሆይ፤ ቀድሞ እንዳደረግኸው የጽድቅ ሥራህ ሁሉ፣ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም፣ ከቅዱሱም ተራራህ ቊጣህን መልስ፤ በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችን በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ዘንድ መሣለቂያ ሆነዋል።

17. “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ።

18. አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው።

19. ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።”

20. እኔም እየተናገርሁና እየጸለይሁ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኀጢአት እየተናዘዝሁ፣ ስለ ቅዱስ ተራራውም እግዚአብሔር አምላኬን እየለመንሁ፤

21. እየጸለይሁም ሳለሁ፣ በመጀመሪያው ራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ በፍጥነት እየበረረ ወደ እኔ መጣ።

22. እርሱም እንዲህ ብሎ አስረዳኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ መጥቻለሁ።

23. አንተ እጅግ የተወደድህ ስለ ሆንህ፣ ገና መጸለይ ስትጀምር መልስ ተሰጥቶአል፤ እኔም ይህን ልነግርህ መጣሁ። ስለዚህ መልእክቱን ልብ በል፤ ራእዩንም አስተውል።

24. “ዐመፃን ለማስቆም፣ ኀጢአትን ለማስወገድ፣ በደልን ለማስተሰረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራእይንና ትንቢትን ለማተምና፣ እጅግ ቅዱስ የሆነውን ለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔ ታውጇል።

25. “ይህንን ዕወቅ፤ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል። ኢየሩሳሌም ከጐዳናዎቿና ከቅጥሮቿ ጋር ትታደሳለች፤ ይህ የሚሆነው ግን በመከራ ጊዜ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 9