ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 8:8-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኀይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ።

9. ከእነዚህም ቀንዶች መካከል በአንዱ ላይ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ መልካሚቱ ምድር በኀይል አደገ።

10. ወደ ሰማይ ሰራዊት እስኪደርስ ድረስ አደገ፤ ከከዋክብት ሰራዊትም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም።

11. ከሰማይ ሰራዊት አለቃ ጋር እስኪተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የልዑሉንም የዘወትር መሥዋዕት ወሰደበት፤ የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ።

12. ከዐመፅ የተነሣም የቅዱሳን ሰራዊት ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለእርሱ አልፎ ተሰጠ፤ የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት፤ እውነትም ወደ ምድር ተጣለች።

13. ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እንዲህ አለው፤ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ ለጥፋት ምክንያት ስለ ሆነው ዐመፅ፣ ከእግር በታች እንዲረገጡ አልፈው ስለሚሰጡት መቅደስና ሰራዊት የታየው ራእይ የሚፈጸመው መቼ ነው?”

14. እርሱም፣ “እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ምሽቶችና ማለዳዎች ድረስ ይቈያል፤ ከዚያም መቅደሱ እንደ ገና ይነጻል” አለኝ።

15. እኔ ዳንኤል ራእዩን ስመለከትና ሳስተውል ሳለ፣ ሰውን የሚመስል ከፊት ለፊቴ ቆመ፤

16. ከኡባልም፣ “ገብርኤል ሆይ፤ ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጒም ንገረው” ብሎ የሚጮኽ የሰው ድምፅ ሰማሁ።

17. እኔ ወደ ቆምሁበት ስፍራ እየቀረበ ሲመጣ፣ ደንግጬ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ራእዩ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እንደሆነ አስተውል” አለኝ።

18. እየተናገረኝ ሳለ፣ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ በከባድ እንቅልፍም ተዋጥሁ፤ እርሱ ግን ዳሰሰኝና በእግሮቼ አቆመኝ።

19. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ራእዩ በመጨረሻው ዘመን ሊሆን ያለውን የሚያመለክት ስለ ሆነ፣ በኋላ በቊጣው ዘመን ምን እንደሚሆን እነግርሃለሁ፤

20. ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል።

21. ጠጒራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው።

22. የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶች፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታት ያመለክታሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም።

23. “በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል።

24. እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኀይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኀያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል።

25. እያጭበረበረ ይበለጽጋል፤ ራሱንም ታላቅ አድርጎ ይቈጥራል። በሰላም ተደላድለን ተቀምጠናል ሲሉ፣ ብዙዎችን ያጠፋል፤ በልዑላን ልዑልም ላይ ይነሣል፤ ይሁን እንጂ እርሱም ይጠፋል፤ ነገር ግን በሰው ኀይል አይደለም።

26. “የተሰጠህ የምሽቱና የማለዳው ራእይ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ የሚሆነውን ስለሚያመለክት ራእዩን ዝጋው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 8