ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እኔም፣ ሜዶናዊው ዳርዮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ እርሱን ለማገዝና ለማበረታታት በአጠገቡ ቆሜ ነበር።

2. “አሁንም እውነቱን እነግርሃለሁ፤ እነሆ፣ ሦስት ሌሎች ነገሥታት በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል። በባለጠግነቱም እጅግ በበረታ ጊዜ፣ ሌላውን ሁሉ አሳድሞ በግሪክ መንግሥት ላይ ያስነሣል።

3. ከዚያም በታላቅ ኀይል የሚገዛና የወደደውንም ሁሉ የሚያደርግ ኀያል ንጉሥ ይነሣል።

4. በኀይል እየገነነ ሳለም፣ መንግሥቱ ይፈርሳል፤ ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳትም ይከፋፈላል። መንግሥቱ ተወስዶ ለሌሎች ስለሚሰጥ፣ ለዘሩ አይተላለፍም፤ ኀይሉም እንደ መጀመሪያው አይሆንም።

5. “የደቡቡ ንጉሥ ይበረታል፤ ነገር ግን ከጦር አዛዦቹ አንዱ ከእርሱ የበለጠ የበረታ ይሆናል፤ ግዛቱም ታላቅ ይሆናል።

6. ከጥቂት ዓመታት በኋላም አንድነት ይፈጥራሉ። የደቡቡ ንጉሥ ሴት ልጅ ስምምነት ለማድረግ ወደ ሰሜኑ ንጉሥ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ኀይሏን ይዛ መቈየት አትችልም፤ እርሱም ሆነ የእርሱ ኀይል አይጸናም። በእነዚያ ቀናት እርሷ ከቤተ መንግሥት አጃቢዎቿ፣ ከአባቷና ከደጋፊዎቿ ጋር ዐልፋ ትሰጣለች።

7. “ከዘመዶቿ አንዱ ስፍራዋን ሊይዝ ይነሣል፤ የሰሜንን ንጉሥ ሰራዊት ይወጋል፤ ምሽጎቹንም ጥሶ ይገባል፤ ከእነርሱም ጋር ተዋግቶ ድል ያደርጋል።

8. አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብፅም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ከመዋጋት ይቈጠባል።

9. የሰሜኑም ንጉሥ፣ የደቡቡን ንጉሥ ግዛት ይወራል፤ ነገር ግን አፈግፍጎ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

10. ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እስከ ጠላት ምሽግ ደርሶ የሚዋጋና ሊቋቋሙት እንደማይቻል ጐርፍ የሚጠራርግ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባሉ።

11. “ከዚያም የደቡቡ ንጉሥ በቊጣ ወጥቶ የሰሜኑን ንጉሥ ይወጋል። የሰሜኑ ንጉሥ ታላቅ ሰራዊት ቢያሰባስብም ይሸነፋል።

12. የደቡቡ ንጉሥ ብዙ ሰራዊት በሚማርክበት ጊዜ ልቡ በትዕቢት ይሞላል፤ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችንም ይገድላል፤ ነገር ግን በድል አድራጊነቱ አይጸናም።

13. የሰሜን ንጉሥ ከመጀመሪያው የሚበልጥ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባል፤ ከብዙ ዓመትም በኋላ በትጥቅ እጅግ ከተደራጀ ታላቅ ሰራዊት ጋር ተመልሶ ይመጣል።

14. “በዚያም ዘመን ብዙዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ራእዩ ይፈጸም ዘንድ፣ ከሕዝብህ መካከል ዐመፀኛ የሆኑ ሰዎች ይነሣሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም።

15. የሰሜኑም ንጉሥ መጥቶ የዐፈር ድልድል ይክባል፤ የተመሸገችውንም ከተማ ይይዛል። የደቡቡ ሰራዊትም ለመቋቋም ኀይል ያጣል፤ የተመረጡት ተዋጊዎቻቸው እንኳ ጸንተው መዋጋት አይችሉም።

16. ወራሪው ደስ ያሰኘውን ያደርጋል፤ ማንም ሊቋቋመው አይችልም። በመልካሚቱ ምድር ላይ ይገዛል፤ እርሷን ለማጥፋትም ኀይል ይኖረዋል።

17. በመንግሥቱ ያለውን ሰራዊት ሁሉ ይዞ ለመምጣት ይወስናል፤ ከደቡብም ንጉሥ ጋር ይስማማል፤ ይህንም መንግሥት ለመጣል ሴት ልጁን ይድርለታል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ አይሳካለትም፤ ያሰበውም ነገር አይጠቅመውም።

18. ከዚህም በኋላ በባሕር ጠረፍ ወዳሉት አገሮች ፊቱን በመመለስ ብዙዎቹን ይይዛል፤ ነገር ግን አንድ አዛዥ ትዕቢቱን ያከሽፍበታል፤ በራሱም ላይ ይመልስበታል።

19. በገዛ አገሩ ወዳሉት ምሽጎችም ፊቱን ይመልሳል፤ ነገር ግን ተሰናክሎ ይወድቃል፤ ዳግምም አይታይም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11