ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 8:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣

7. ቊራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቊራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።

8. ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤

9. ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት።

10. ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት።

11. እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጒደሉን ዐወቀ።

12. ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም።

13. ኖኅ በተወለደ በ601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ።

14. ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።

15. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን እንዲህ አለው፤

16. “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ።

17. እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋር ያሉትን እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”

18. ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 8