ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 30:28-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ይልቅስ ይገባኛል የምትለውን ደሞዝ ንገረኝና እከፍልሃለሁ።”

29. ያዕቆብም እንዲህ አለው፤ “መቼም እንዴት እንዳገለገልሁህ፣ ከብቶችህ በእኔ ጥበቃ ምን ያህል እንደ ተመቻቸው አንተ ታውቃለህ።

30. እኔ ከመምጣቴ በፊት ጥቂት የነበረው ሀብትህ ዛሬ ተትረፍርፎአል፣ በተሰማራሁበት ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) በረከቱን አብዝቶልሃል። ታዲያ፣ ስለ ራሴ ቤት የማስበው መቼ ነው?”

31. ላባም፣ “ታዲያ ምን ልስጥህ?” ሲል ጠየቀው።ያዕቆብም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ምንም አትስጠኝ፤ ነገር ግን የምጠይቅህን አንዲት ነገር ብቻ ብታደርግልኝ ከብቶችህን ማገዴን እቀጥላለሁ፤

32. በመንጎቹ መካከል ዛሬ ልዘዋወርና ከበጎቹ መካከል ዝንጒርጒር የሆኑትን፣ ነቍጣ ያለባቸውንና ጥቋቁሮቹን እንዲሁም ከፍየሎቹ ነቍጣ ያለባቸውንና ዝንጒርጒሮቹን ልምረጥ፤ እነዚህ ደሞዜ ይሁኑ።

33. ወደ ፊት ደሞዜን ለመቈጣጠር በምትመጣበት ጊዜ ታማኝነቴ ይታወቃል፤ በመንጎቼ መካከል ዝንጒርጒር ወይም ነቍጣ የሌለበት ፍየል፣ ወይም ጥቁር ያልሆነ ቢገኝ ያ እንደ ተሰረቀ ይቈጠር”።

34. ላባም፣ “እሺ፣ ይሁን፤ ባልኸው ተስማምቼአለሁ” አለው።

35. ነገር ግን በዚያኑ ዕለት ከተባት ፍየሎች ሽመልመሌ የሆኑትን ወይም ነቍጣ ያለባቸውን ሁሉ፣ እንዲሁም ከእንስት ፍየሎች ነቍጣ ያለባቸውን ዝንጒርጒር የሆኑትን ሁሉ፣ ማንኛውንም ነጭ ያለበትን ሁሉ መረጠ፤ ደግሞም ጥቋቁር የሆኑትንም በጎች ሁሉ ለየና ወንዶች ልጆቹን አስጠበቃቸው።

36. ከዚያም በእርሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ማገዱን ቀጠለ።

37. ነገር ግን ያዕቆብ እርጥብ የልብን፣ የለውዝንና የኤርሞን በትሮች ወሰደ፤ ቅርፊታቸውንም በቀጭን ልጦ እያነሣ የበትሮቹ ግንድ ነጩ እንዲታይ፣ ሽመልመሌ መልክ እንዲኖራቸው አደረገ።

38. የላጣቸውንም በትሮች መንጎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው በማጠጫ ገንዳዎቹ ሁሉ አስቀመጠ። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣

39. በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ።

40. ያዕቆብ ግልገሎቹን ለብቻ ለያቸው፤ የቀሩትንም የላባ መንጎች ሽመል መሌና ጥቋቁር በሆኑት ትይዩ አቆማቸው፤ በዚህም መሠረት የራሱ መንጋ ከላባ መንጋ ጋር እንዳይቀላቀል ለብቻ ለየ።

41. ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠ በጡበት ጊዜ፣ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎቹ ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤

42. ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን፣ በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ።

43. በዚህም ሁኔታ ይህ ሰው እጅግ ባለጠጋ ሆነ፤ የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 30