ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 25:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይስሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው።

7. አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ።

8. ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

9. ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤

10. ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ።

11. አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይስሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይስሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር።

12. ግብፃዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው።

13. የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦ የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣ ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣

14. ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣

15. ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣ ናፌስና ቄድማ።

16. እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈ ሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው።

17. እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

18. ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብፅ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖሩ።

19. የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድ ይህ ነው፤አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤

20. ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 25