ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 25:15-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣ ናፌስና ቄድማ።

16. እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈ ሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው።

17. እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

18. ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብፅ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖሩ።

19. የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድ ይህ ነው፤አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤

20. ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች።

21. ይስሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች።

22. ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለመጠየቅ ሄደች።

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አላት፤“ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት።

24. የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀንዋ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ።

25. በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጒር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ።

26. ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይስሐቅ የሥልሳ ዓመት ሰው ነበር።

27. ልጆቹም አደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 25