ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 21:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ።

6. ሣራም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይሥቃል” አለች።

7. ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች።

8. ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ።

9. በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፣ በይስሐቅ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤

10. አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርልኝ፤ ምንም ቢሆን የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ውርስ አይካፈልም አለች።”

11. እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው።

12. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ።

13. የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።”

14. በማግስቱ አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሞአት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር።

15. በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቊጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው።

16. ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር።

17. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ።

18. ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።”

19. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጒድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።

20. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከልጁ ጋር ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 21