ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 8:13-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጒንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየአጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ።

14. በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች።

15. ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።

16. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው።

17. እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው።

18. ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም። ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር።

19. አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።

20. ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

21. ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብፃውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 8