ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 39:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ልክ ከኤፉዱ መታጠቂያ በላይ፣ ከመጋጠሚያው አጠገብ፣ ከኤፉዱ ፊት ለፊት ካሉት ከትከሻ ንጣዮች ጋር አያያዟቸው።

21. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ተነጥሎ ለብቻው እንዳይንጠለጠል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከመታጠቂያው ጋር በማገናኘት፣ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ፈትል አሠሯቸው።

22. የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ሠሩት፤

23. ይህም እንደ ክሳዱ ቅድ ከቀሚሱ መካከል ላይ አንገትጌ ነበረው፤ እንዳይተረተርም በአንገትጌው ዙሪያ ላይ ቅምቅማት ነበረው።

24. በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ላይ ሮማኖቹን አደረጉ።

25. ከንጹሕ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ እነዚህንም በሮማኖቹ መካከል በጠርዙ ዙሪያ አደረጉ።

26. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ለአገልግሎት ይለበሱ ዘንድ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ላይ ተሰባጥረው ይገኙ ነበር።

27. ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የሸማኔ ሥራ የሆነውን ከቀጭን በፍታ ሸሚዞችን ሠሩ፤

28. እንዲሁም ከቀጭን በፍታ ጥምጥምን፣ የሐር ቆቦቹንና በቀጭኑ ከተፈተለም በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ።

29. መታጠቂያው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ የጥልፍ ጠላፊ ሥራ ሆኖ የተሠራ ነበረ።

30. ከንጹሕ ወርቅ የተቀደሰውን አክሊል ሰሌዳ ሠርተው፣ በማኅተም ላይ እንደ ተቀረጸ ጽሑፍ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)” የሚል ቀረጹበት፤

31. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ከመጠምጠሚያው ጋር ለማያያዝ ሰማያዊ ፈትል አሠሩበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 39