ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 30:2-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ርዝመቱና ጐኑ ባለ አንድ አንድ ክንድ የሆነ ከፍታውም ሁለት ክንድ የሆነ አራት ማእዘን ይሁን፤ ከመሠዊያው ጋር አንድ ወጥ የሆኑ ቀንዶች ይኑሩት።

3. ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለብጣቸው፤ ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።

4. መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙ፣ ከክፈፉ በታች ትይዩ የሆኑ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ለመሠዊያው አብጅ።

5. መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።

6. መሠዊያውን ከመጋረጃው ፊት ለፊት፣ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት፣ ከምስክሩ በላይ ካለው እኔ አንተን ከምገናኝበት ከስርየት መክደኛው ፊት አስቀምጠው።

7. “አሮን መብራቶቹን በሚያዘጋጅበት ጊዜ፣ በየማለዳው ደስ የሚያሰኝ ሽታ ዕጣን በመሠዊያው ላይ ያጢስ።

8. ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው።

9. በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስበት።

10. አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርግበታል፤ ይህ ዓመታዊ ማስተስረያ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለማስተስረያ ከሚሆን የኀጢአት መስዋዕት ደም ጋር መደረግ አለበት፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅግ ቅዱስ ነው።”

11. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

12. “የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም።

13. ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅል መስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

14. ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው።

15. ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለ ጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጉድሎ አይስጥ።

16. የማስተሰረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።”

17. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 30