ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 26:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ቀለበቶችን ትይዩ በማድረግ አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው ጠርዝ መጋረጃ፣ አምሳ ቀለበቶችንም በሌላው ጠርዝ መጋረጃ አድርግ።

6. ከዚያም የመገናኛው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድ መጋረጃዎቹን በአንድ ላይ ለማያያዝ አምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሥራ።

7. “ማደሪያ ድንኳኑን ከላይ ሆነው የሚሸፍኑ ዐሥራ አንድ የፍየል ጠጒር መጋረጃዎች ሥራ።

8. ዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች እኩል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ ርዝመት ሠላሳ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

9. አምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ፣ እንደዚሁም ስድስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ አድርገህ ስፋቸው፤ ከማደሪያው ድንኳን ፊት ለፊት ስድስተኛውን መጋረጃ እጠፍና በላዩ ላይ ደርበው።

10. በአንድ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን አድርግ።

11. ከዚያም አምሳ የናስ ማያያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝ በቀለበቶቹ ውስጥ ጨምራቸው።

12. ስለ ድንኳኑ መጋረጃዎች ትርፍ ቁመትም፣ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ላይ እንዲንጠለጠል ይሁን።

13. የድንኳኑ መጋረጃዎች በሁለቱም ጐኖች አንድ ክንድ ርዝመት ይኖራቸዋል፤ የተረፈውም የማደሪያውን ድንኳን ጎኖች እንዲሸፍን ሆኖ ይንጠለጠላል፤

14. ለድንኳኑ በቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ልብስ አብጅ፤ በላዩም ላይ የአቆስጣ ቆዳ ይሁን።

15. “ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አብጅ።

16. እያንዳንዱም ወጋግራ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ተኵል ይሁን፤

17. ሁለት ጉጦችም ጎን ለጎን ይሁኑለት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች ሁሉ በዚሁ መልክ አብጅ

18. ለማደሪያው ድንኳን ክፍል ሃያ ወጋግራዎችን ሥራ።

19. ከሥራቸው የሚሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ፤ በእያንዳንዱ ጒጠት ሥር አንድ መቆሚያ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ይኑሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 26