ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 17:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ስለዚህ፣ “የምንጠጣውን ውሃ ስጠን” በማለት ሙሴን ተጣሉት።ሙሴም፣ “እኔን ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ (ያህዌ) ለምን ትፈታተኑታላችሁ?” አለ።

3. ነገር ግን ሕዝቡ በዚያ ተጠምተው ስለ ነበር፣ በሙሴ ላይ አጒረመረሙ። እነርሱም፣ “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውሃ ጥም እንድናልቅ፣ ከግብፅ ለምን አወጣኸን?” አሉት።

4. ከዚያም ሙሴ፤ “በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” ብሎ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።

5. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንዲህ መለሰለት፤ “ከሕዝቡ ፊት ሂድ፤ ከእስራኤል አለቆች አንዳንዶቹን እንዲሁም አባይን የመታህባትን በትር ያዝና ሂድ።

6. ኮሬብ አጠገብ ባለው ዐለት በዚያ እኔ በአንተ ፊት እቆማለሁ። ዐለቱን ምታው፤ ከእርሱም ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ይወጣል።” ስለዚህ ሙሴ በእስራኤል አለቆች ፊት ይህንኑ አደረገ።

7. ስፍራውንም ማሳህና መሪባ ብሎ ጠራው፤ እስራኤላውያን ጠብ ፈጥረው፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም” በማለት እግዚአብሔርን (ያህዌ) ተፈታትነዋልና።

8. አማሌቃውያን መጥተው እስራኤላውያንን ራፊዲም ላይ ወጉ፤

9. ሙሴም ኢያሱን፣ “ከሰዎቻችን አንዳንዶቹን ምረጥና አማሌቃውያንን ለመውጋት ውጣ፤ በነገው ዕለት የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) በትር በእጆቼ ይዤ በኰረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ።”

10. ስለዚህ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ከአማሌቃውያን ጋር ተዋጋ፤ ሙሴ፣ አሮንና ሖርም ወደ ኰረብታው ጫፍ ወጡ።

11. ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ በሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር።

12. የሙሴ እጆች እየዛሉ በሄዱ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከበታቹ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በአንዱ በኩል ሌላውም በሌላ በኩል ሆነው እጆቹን ወደ ላይ ያዙ። ይኸውም እጆቹ ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ጸንተው እንዲቆዩ ነው።

13. ስለዚህ ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ።

14. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈፅሜ እደመስሳለሁ” አለው።

15. ሙሴም መሠዊያውን ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አርማዬ ነው” ብሎ ሰየመው።

16. “እጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዙፋን ተዘርግተዋልና፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አማሌቃውያንን ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋቸዋል” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 17