ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 9:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብፅ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፅህ ነህ።

8. በኮሬብ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለቊጣ አነሣሣችሁት፤ እርሱም እናንተን ሊያጠፋችሁ እጅግ ተቈጣ።

9. እኔም የድንጋይ ጽላቶቹን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን የኪዳን ጽላቶች ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ፣ እህል ሳልበላ፣ ውሃም ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤

10. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁበት ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ከተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ትእዛዛት ሁሉ በእነርሱ ላይ ነበሩባቸው።

11. አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ማለትም የኪዳኑን ጽላቶች ሰጠኝ።

12. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ተነሣ፤ ከግብፅ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ረክሰዋልና ፈጥነህ ከዚህ ውረድ፤ እኔ ካዘዝኋቸው ፈጥነው ፈቀቅ ብለዋል፤ ቀልጦ የተሠራ ጣዖትም ለራሳቸው አበጅተዋል” ብሎ ነገረኝ።

13. ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ሕዝብ አይቼዋለሁ፤ በእርግጥ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው፣

14. አጠፋቸውና ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ብዙ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 9