ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 29:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም።

6. ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) እንደሆንሁ ታውቁ ዘንድ ነው።

7. ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፣ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።

8. ምድራቸውንም ወስደን፤ ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን።

9. እንግዲህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወ ንላችሁ፣ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ።

10. እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፣ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ቆማችኋል፤

11. ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ እንጨትህን እየፈለጡ፣ ውሃህንም እየቀዱ በሰፈርህ የሚኖሩ መጻተኞችም አብረውህ ቆመዋል።

12. እዚህ የቆምኸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ከአንተ ጋር ወደሚያደርገውና በመሓላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከአምላክህከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ጋር ትገባ ዘንድ፣

13. ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ (ኤሎሂም) ይሆን ዘንድ፣ አንተም ሕዝቡ መሆንህን፣ በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው።

14. እኔም ይህን የመሓላ ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤

15. አብራችሁን በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት እዚህ ከቆማችሁት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ ከሌሉትም ጋር ነው።

16. በግብፅ ምድር እንዴት እንደኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

17. በመካከላቸውም አስጸያፊ ምስሎቻቸውንና የዕንጨትና የድንጋይ፣ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል።

18. የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚመልስ ወንድም ሆነ ሴት ጐሣም ሆነ ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ አለመገኘቱን አረጋግጡ፤ ከመካከልህ እንዲህ ያለውን መራራ መርዝ የሚያወጣ ሥር እንዳይኖር ተጠንቀቁ።

19. እንዲህ ያለው ሰው የዚህን መሐላ ቃል በሚሰማበት ጊዜ፣ በልቡ ራሱን በመባረክ፣ “እንደ ልቤ ሐሳብ ብኖርም እንኳ ሰላም አለኝ” ብሎ ያስባል። ይህም በለምለሙም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ጥፋትን ያመጣል።

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግለትም፤ ቊጣውና ቅናቱ በእርሱ ላይ ይነድበታል። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 29