ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የቃል ኪዳኑ መታደስ

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋር እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።

2. ሙሴ እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ፣ በፈርዖን፣ በሹማምቱ ሁሉና በመላ አገሩ ላይ ያደረገውን ሁሉ ዐይኖቻችሁ አይተዋል።

3. እነዚያን ከባድ ፈተናዎች፣ ታምራዊ ምልክቶችና ታላላቅ ድንቆች በገዛ ዐይኖቻችሁ አይታችኋል።

4. ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።

5. በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም።

6. ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) እንደሆንሁ ታውቁ ዘንድ ነው።

7. ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፣ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።

8. ምድራቸውንም ወስደን፤ ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን።

9. እንግዲህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወ ንላችሁ፣ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ።

10. እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፣ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ቆማችኋል፤

11. ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ እንጨትህን እየፈለጡ፣ ውሃህንም እየቀዱ በሰፈርህ የሚኖሩ መጻተኞችም አብረውህ ቆመዋል።

12. እዚህ የቆምኸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ ከአንተ ጋር ወደሚያደርገውና በመሓላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከአምላክህከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ጋር ትገባ ዘንድ፣

13. ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ (ኤሎሂም) ይሆን ዘንድ፣ አንተም ሕዝቡ መሆንህን፣ በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው።

14. እኔም ይህን የመሓላ ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤

15. አብራችሁን በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት እዚህ ከቆማችሁት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ ከሌሉትም ጋር ነው።

16. በግብፅ ምድር እንዴት እንደኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

17. በመካከላቸውም አስጸያፊ ምስሎቻቸውንና የዕንጨትና የድንጋይ፣ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል።

18. የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚመልስ ወንድም ሆነ ሴት ጐሣም ሆነ ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ አለመገኘቱን አረጋግጡ፤ ከመካከልህ እንዲህ ያለውን መራራ መርዝ የሚያወጣ ሥር እንዳይኖር ተጠንቀቁ።

19. እንዲህ ያለው ሰው የዚህን መሐላ ቃል በሚሰማበት ጊዜ፣ በልቡ ራሱን በመባረክ፣ “እንደ ልቤ ሐሳብ ብኖርም እንኳ ሰላም አለኝ” ብሎ ያስባል። ይህም በለምለሙም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ጥፋትን ያመጣል።

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግለትም፤ ቊጣውና ቅናቱ በእርሱ ላይ ይነድበታል። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።

21. በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።

22. የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ።

23. ምድሪቱ በሙሉ የተቃጠለ ጨውና ዲን ዐመድ ትሆናለች። አንዳች ነገር አይተከልባትም፤ ምንም ነገር አያቈጠቊጥባትም፤ የሚያድግ ተክል አይገኝባትም። የሚደርስባት ውድመት እግዚአብሔር (ያህዌ) በታላቅ ቊጣ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፣ እንደ አዳማና ሲባዮ ጥፋት ይሆናል።

24. አሕዛብም ሁሉ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪና የሚነድ ቊጣስ ለምን መጣባት?” ብለው ይጠይቃሉ።

25. መልሱም፣ “የአባቶቻቸው አምላክ (ኤሎሂም) ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ፣ ከእነርሱ ጋር የገባውን ኪዳን ሕዝቡ ስለ ተዉ ነው።

26. ወጥተውም የማያውቋቸውን፣ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም።

27. ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣባት ድረስ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ በዚህች ምድር ላይ ነደደ።

28. በአስፈሪ ቊጣና በታላቅ መዓት እግዚአብሔር (ያህዌ) ከምድራቸው ነቀላቸው፤ አሁን እንደሆነውም ወደ ሌላ ምድር ጣላቸው” የሚል ይሆናል።

29. ምስጢር የሆነው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ እንከተል ዘንድ ለዘላለም የኛና የልጆቻችን ነው።