ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘካርያስ 1:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤

15. ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’

16. “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ በዚያም ቤቴ እንደ ገና ይሠራል፤ መለኪያ ገመድም በኢየሩሳሌም ላይ ይዘረጋል’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።’

17. “ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”

18. ከዚያም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ ከፊቴም አራት ቀንዶችን አየሁ፤

19. ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ፣ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት።እርሱም፣ “እነዚህ ይሁዳን፣ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው” አለኝ።

20. ከዚያም እግዚአብሔር አራት የእጅ ሙያተኞችን አሳየኝ።

21. እኔም፣ “እነዚህስ ምን ሊያደርጉ መጡ?” አልሁ።እርሱም፣ “እነዚህ ቀንዶች ማንም ራሱን ቀና ማድረግ እንዳይችል ይሁዳን የበታተኑ ናቸው፤ እነዚህ የእጅ ሙያተኞች ግን የመጡት እነርሱን ሊያስደነግጧቸው፣ ሕዝቡን ለመበታተን በይሁዳ ምድር ላይ ቀንዳቸውን ያነሡትን የእነዚህን የአሕዛብ ቀንዶች ሰብሮ ለመጣል ነው” አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘካርያስ 1