ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 5:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ካህኑ ሴትየዋን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድትቆም ካደረገ በኋላ የጠጒሯን መሸፈኛ ይገልጣል፤ ስለ ቅናት የቀረበውን የመታሰቢያ ቍርባን በእጇ ያስይዛታል፤ ከዚያም ካህኑ ርግማን የሚያመጣውን መራራ ውሃ በእጁ ይይዛል።

19. ካህኑም ሴትየዋን ያስምላታል፤ እንዲህም ይላታል፤ “ሌላ ወንድ አብሮሽ ካልተኛ በትዳር ላይ ሆነሽ ወደ ርኩሰት ካላዘነበልሽ ይህ ርግማን የሚያመጣ መራራ ውሃ ጒዳት አያድርስብሽ፤

20. ነገር ግን በትዳር ላይ እያለሽ ወደ ርኵሰት በማዘንበል ከባልሽ ሌላ ከወንድ ጋር በመተኛት ከጐደፍሽ”፣

21. እዚህ ላይ ካህኑ እንዲህ በማለት ሴትየዋን በርግማን መሐላ ያስምላታል፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ጭንሽን እያሰለለና ሆድሽን እያሳበጠ በሕዝብሽ መካከል ርግማንና መሐላ ያድርግብሽ፤

22. ይህን ርግማን የሚያመጣ ውሃ በጠጣሽ ጊዜም ሆድሽን ያሳብጠው፤ ጭንሽን ያሰልለው፤”“ ‘ሴትዮዋም፣ “አሜን፤ አሜን” ትበል።

23. “ ‘ካህኑ እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጻፍ፤ በመራራውም ውሃ ይደምስሳቸው።

24. ርግማን የሚያመጣውንም ውሃ ሴትየዋ እንድትጠጣ ያድርግ፤ ውሃውም ወደ ሰውነቷ ገብቶ የመረረ ሥቃይ ያስከትልባታል።

25. ካህኑ ለቅናት የቀረበውን የእህል ቊርባን ይቀበላት፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዝውዞ ወደ መሠዊያው ያቅርበው።

26. ካህኑ የመታሰቢያ ቊርባን እንዲሆን እፍኝ የእህል ቍርባን ከዚያ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ከዚያም በኋላ ሴቲቱ ውሃውን እንድትጠጣ ያድርግ።

27. ራሷን በማጒደፍ ለባሏ ያላትን ታማኝነት አጒድላ ከሆነ፣ ርግማን የሚያመጣውን ውሃ እንድትጠጣ ሲደረግ ውሃው ወደ ሰውነቷ ገብቶ ክፉ ሥቃይ ያመጣባታል፤ ሆዷ ያብጣል፤ ጭኗ ይሰልላል፤ በሕዝቦቿም ዘንድ የተረገመች ትሆናለች።

28. ዳሩ ግን ሴትየዋ ካልጐደፈችና ነውር ከሌለባት ከበደሉ ነጻ ትሆናለች፤ ልጆችም ትወልዳለች።

29. “ ‘እንግዲህ የቅናት ሕግ ይህ ነው፤ አንዲት ሴት በትዳር ላይ እያለች ወደ ሌላ ሄዳ ከረከሰች፣

30. ወይም አንድ ሰው ሚስቱን ከመጠርጠሩ የተነሣ የቅናት መንፈስ ሲያድርበት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቁማት፤ ካህኑም ሕጉ በሙሉ በሴቲቱ ላይ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያድርግ።

31. ባልየውም ከበደል ንጹሕ ይሆናል፤ ሴትዮዋ ግን በበደሏ ምክንያት የሚመጣውን ፍዳ ትቀበላለች።” ’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 5