ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 28:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር አብሮት የሚቀርበውም የመጠጥ ቊርባን ፈልቶ የወጣለት የሂን አንድ አራተኛ መጠጥ ይሆናል፤ የመጠጡንም ቊርባን በተቀደሰው ቦታ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍስሱት።

8. ሁለተኛውንም ጠቦት ጠዋት ባቀረባችሁት ዐይነት አድርጋችሁ ከእህል ቊርባኑና ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር ማታ አቅርቡት፤ ይህም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

9. “ ‘በሰንበት ዕለት፣ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የማይገኝባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መሥዋዕት ከመጠጥ ቊርባኑና በዘይት ከተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ጋር አቅርቡ።

10. ይህም ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ በየሰንበቱ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

11. “ ‘በየወሩ መባቻ እንከን የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።

12. ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤

13. እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

14. ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን የኢን ግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢን አንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

15. ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይቀርባል።

16. “ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይከበራል።

17. በዚሁ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብሉ።

18. በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አትሥሩበት።

19. እንከን የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።

20. ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤

21. ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 28