ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 26:46-63 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

46. አሴር ሤራሕ የምትባል ልጅ ነበረችው።

47. እነዚህ የአሴር ጐሣዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።

48. የንፍታሌም ዘሮች በየጐሣቸው እነዚህ ነበሩ፤በያሕጽኤል በኩል፣ የያሕጽኤላውያን ጐሣ፣በጉኒ በኩል፣ የጉናውያን ጐሣ፣

49. በሺሌም በኩል፣ የሺሌማውያን ጐሣ፤

50. እነዚህ የንፍታሌም ጐሣዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።

51. ባጠቃላይ የእስራኤል ወንዶች ቍጥር ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበር።

52. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

53. “ምድሪቱ በስማቸው ቍጥር ልክ ተደልድላ በርስትነት ለእነርሱ ትሰጥ።

54. በርከት ያለ ቊጥር ላለው ጐሣ ሰፋ ያለውን ርስት፣ አነስ ያለ ቊጥር ላለው ጐሣ ደግሞ አነስ ያለውን ስጥ፤ ርስቱንም እያንዳንዱ በዝርዝሩ ላይ በተመለከተው ቊጥር መሠረት ይረከባል።

55. የመሬት ድል ድሉም በዕጣ ይሁን፤ እያንዳንዱ የሚወርሰውም በየነገድ አባቶቹ ስም ይሆናል።

56. እያንዳንዱም ርስት በትል ልቆቹና በትንንሾቹ ነገዶች መካከል በዕጣ ይደለደላል።

57. በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሌዋውያን እነዚህ ነበሩ፤በጌድሶን በኩል፣ የጌድሶናውያን ጐሣ፣በቀዓት በኩል፣ የቀዓታውያን ጐሣ፣በሜራሪ በኩል፣ የሜራራውያን ጐሣ፤

58. እነዚህም ደግሞ የሌዊ ጐሣዎች ነበሩ፤የሊብናውያን ጐሣ፣የኬብሮናውያን ጐሣ፣የሞሖላውያን ጐሣ፣የሙሳውያን ጐሣ፣የቆሬያውያን ጐሣ።ቀዓት የእንበረም ቅድመ አያት ነበር፤

59. ሚስቱ ዮካብድ ትባል ነበር፤ እርሷም በግብፅ አገር ከሌዋውያን የተወለደች የሌዊ ዘር ነበረች። ከእንበረምም አሮንን፣ ሙሴንና እኅታቸውን ማርያምን ወለደች።

60. አሮንም የናዳብና የአብዮድ፣ የአልዓዛርና የኢታምር አባት ነበር።

61. ነገር ግን ናዳብና አብዩድ ባልተፈቀደ እሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ስላቀረቡ ሞቱ።

62. አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ተቈጥረው ሃያ ሦስት ሺህ ሆኑ፤ እነርሱም ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ርስት ተካፋዮች ስላልነበሩ አብረዋቸው አልተቈጠሩም።

63. ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ካለው ከሞዓብ ሜዳ ላይ የእስራኤልን ሕዝብ በቈጠሩበት ወቅት የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 26