ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 15:6-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “ ‘ከአውራ በግ ጋር በኢን ሢሶ ዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አዘጋጁ፤

7. እንዲሁም ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን የኢን አንድ ሦስተኛ የወይን ጠጅ አዘጋጁ፤ ይህንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ ሽታ ያለው አድርጋችሁ አቅርቡ።

8. “ ‘አንዱን ወይፈን ለተለየ ስለት ወይም ለኅብረት የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የዕርድ መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታዘጋጁበት ጊዜ፣

9. ከወይፈኑ ጋር በግማሽ ኢን ዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት አብራችሁ አምጡ።

10. እንዲሁም ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን ግማሽ ኢን የወይን ጠጅ አቅርቡ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብና ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል።

11. እያንዳንዱ ወይፈን ወይም አውራ በግ፣ እያንዳንዱ የበግም ሆነ የፍየል ጠቦት በዚህ ሁኔታ ይዘጋጅ።

12. ባዘጋጃችሁት ቍጥር ልክ ይህን ለእያንዳንዱ አድርጉ።

13. ማናቸውም የአገር ተወላጅ የሆነ በእሳት የሚቀርብ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች በዚሁ ሁኔታ ያድርግ።

14. ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ መጻተኛ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማናቸውም ሰው በእሳት የሚቀርብ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ልክ እናንተ እንደምታደርጉት ያድርግ።

15. ማኅበረ ሰቡ ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ አንድ ዐይነት ደንብ ይኖረዋል፤ ይህም በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ የማይሻር ሥርዐት ነው። እናንተም ሆናችሁ መጻተኞቹ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እኩል ትታያላችሁ፤

16. ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ይኸው ሕግና ሥርዐት እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።’ ”

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

18. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እኔ ወደምወስዳችሁ ምድር ገብታችሁ፣

19. የምድሪቱን በረከት ስትመገቡ ከዚሁ ላይ አንሥታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊርባን አቅርቡ።

20. ይህንም ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ ኅብስት ጋግራችሁ ከዐውድማ እንደ ተገኘ ቊርባን አድርጋችሁ አምጡ።

21. በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ አንሥታችሁ ይህን ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ትሰጣላችሁ።

22. “ ‘እንግዲህ ካለማወቅ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ከሰጣቸው ትእዛዛት አንዱን ሳትፈጽሙ ብትቀሩ፣ ይህም ማለት

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 15