ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 11:22-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?”

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክንድ ይህን ያህል አጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት።

24. ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው።

25. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም።

26. ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ።

27. አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው።

28. ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ።

29. ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ተቈርቍረህ ነውን? የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤

30. ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ።

31. በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣ ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው፤

32. በዚያን ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግሥቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት።

33. ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ።

34. ሌላ ምግብ ለማግኘት የጐመጁትን ሰዎች በዚያ ስለ ቀበሩአቸው የቦታው ስም “ቂብሮት ሃታአባ” ተባለ።

35. ሕዝቡም ከቂብሮት ሃታአባ ወደ ሐጼሮት ተጒዘው እዚያው ሰፈሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 11