ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 23:19-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ።

20. ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋር የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው።

21. በዚያኑ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።

22. “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

24. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በዚሁ በመለከት ድምፅ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ።

25. መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ”

26. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

27. “የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።

28. በእግዚአብሔር (ያህዌ) በአምላካችሁ (ኤሎሂም) ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለ ሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ።

29. በዚያ ዕለት ሰውነቱን የሚያጐሳቊል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።

30. በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።

31. ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው።

32. ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።”

33. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

34. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቆያል።

35. የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።

36. ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 23