ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 23:12-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ነዶውን በምትወዘውዙበት ቀን እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤

13. ከዚህም ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ለእህል ቊርባን፣ አንድ አራተኛ የኢን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቊርባን አቅርቡ።

14. ስጦታውን ለአምላካችሁ (ኤሎሂም) እስከምታቀርቡበት እስከዚያ ቀን ድረስ እንጀራም ቢሆን፣ ቈሎ ወይም እሸት አትብሉ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።

15. “ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቊጠሩ።

16. እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቊጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።

17. በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምጡ።

18. ከእንጀራውም ጋር ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቊርባናቸውና ከመጠጥ ቊርባናቸው ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው።

19. እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ።

20. ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋር የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው።

21. በዚያኑ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።

22. “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

24. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በዚሁ በመለከት ድምፅ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ።

25. መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 23