ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 22:22-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጒንድሽ ወይም ማንኛውንም ዐይነት እከክ ወይም ቋቊቻ ወይም የሚመግል ቊስል ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ፤ ከነዚህ መካከል የትኛውንም በመሠዊያው ላይ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ።

23. አካሉ ከመጠን በላይ የረዘመን ወይም ያጠረን በሬ ወይም በግ የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጋችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ይሁን እንጂ ስእለት ለመፈጸም ተቀባይነት አይኖረውም፤

24. አባለዘሩ የተቀጠቀጠ ወይም የተኰላሸ፣ የተሰነጠቀ ወይም የተቈረጠ ማንኛውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ፤ እነዚህንም በምድራችሁ አትሠው።

25. እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ከባዕዳን በመቀበል ለአምላካችሁ (ኤሎሂም) ምግብ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ ነውር ስላለባቸው ፍጹም አይደሉምና ተቀባይነት አይኖራቸውም።’ ”

26. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

27. “ጥጃ ወይም የበግ ግልገል ወይም የፍየል ግልገል በሚወለድበት ጊዜ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቈይ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ግን ተቀባይነት ያለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ይሆናል።

28. ላምን ከጥጃዋ፣ በግንም ከግልገሏ ጋር በአንድ ቀን አትረዱ።

29. “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጋችሁ አቅርቡት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 22