ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 22:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ነገር ግን ካህኑ በገንዘብ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ ባሪያ ቢኖረው፣ ያ ባሪያ ከካህኑ ድርሻ መብላት ይችላል።

12. የካህን ልጅ፣ ካህን ያልሆነ ሌላ ሰው ካገባች፣ ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አትችልም።

13. ይሁን እንጂ የካህኑ ልጅ ባሏ ቢሞት ወይም ብትፋታ፣ ልጆችም ባይኖሩዋትና እንደ ልጅነት ጊዜዋ በአባቷ ቤት ለመኖር ብትመለስ፣ ከአባቷ ድርሻ መብላት ትችላለች፤ ያልተፈቀደለት ሰው ግን ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አይችልም።

14. “ ‘ማንኛውም ሰው ባለማወቅ የተቀደሰውን መሥዋዕት ቢበላ፣ የመሥዋዕቱን አንድ አምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይተካ።

15. እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡትን የተቀደሰ መሥዋዕት ካህናቱ አያርክሱት፤

16. ይህንኑ የተቀደሰ መሥዋዕት እንዲበሉና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽሙ አያድርጉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

18. “ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ከእናንተ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ቢሆን፣

19. መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው ከላም ወገን ወይም ከበጎች ወይም ከፍየሎች እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ።

20. እንከን ያለበትን ማንኛውንም ነገር አታቅርቡ፤ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት አይኖረውምና።

21. ማንኛውም ሰው ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ከላም ወይም ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት ሲያቀርብ፣ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ፍጹም የሆነውንና ነውር የሌለበትን ያቅርብ።

22. ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጒንድሽ ወይም ማንኛውንም ዐይነት እከክ ወይም ቋቊቻ ወይም የሚመግል ቊስል ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ፤ ከነዚህ መካከል የትኛውንም በመሠዊያው ላይ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ።

23. አካሉ ከመጠን በላይ የረዘመን ወይም ያጠረን በሬ ወይም በግ የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጋችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ይሁን እንጂ ስእለት ለመፈጸም ተቀባይነት አይኖረውም፤

24. አባለዘሩ የተቀጠቀጠ ወይም የተኰላሸ፣ የተሰነጠቀ ወይም የተቈረጠ ማንኛውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ፤ እነዚህንም በምድራችሁ አትሠው።

25. እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ከባዕዳን በመቀበል ለአምላካችሁ (ኤሎሂም) ምግብ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ ነውር ስላለባቸው ፍጹም አይደሉምና ተቀባይነት አይኖራቸውም።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 22