ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 7:12-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፤ ለሰማይ አምላክ ሕግ መምህር ለሆነው ለካህኑ ለዕዝራ፤ሰላም ለአንተ ይሁን፤

13. ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖርና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚፈልግ ማንኛውም እስራኤላዊ መሄድ እንዲችል ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

14. በእጅህ በሚገኘው በአምላክህ ሕግ መሠረት፣ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል።

15. ከዚህም በላይ፣ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤

16. እንዲሁም ከመላው ባቢሎን አውራጃ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፣ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው የሚሰጡትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ።

17. በዚህም ገንዘብ ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን፣ ከእህል ቊርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቊርባኖቻቸው ጋር መግዛት እንዳለብህ አትርሳ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ አቅርብ።

18. ከዚህ የሚቀረውንም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ አይሁድ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ደስ ለሚላችሁ ነገር ሁሉ አውሉት።

19. ለአምላክህ ቤተ መቅደስ በዐደራ የተሰጠህንም ዕቃ ሁሉ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ።

20. ከዚህም በላይ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ለመስጠት የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ግምጃ ቤት መውሰድ ትችላለህ።

21. በኤፍራጥስ ማዶ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ፣ የሰማይ አምላክ ሕግ መምህር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት እኔ ንጉሥ አርጤክስስ እነሆ አዝዣለሁ፤

22. እስከ አንድ መቶ መክሊት ብር፣ እስከ አንድ መቶ ቆሮስ ስንዴ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ የወይራ ዘይትና የሚፈለገውን ያህል ጨው ስጡት።

23. የሰማይ አምላክ የሚያዘው ሁሉ፣ ለሰማይ አምላክ ቤተ መቅደስ በፍጹም ትጋት ይደረግ፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ለምን ቊጣ ይውረድ?

24. ደግሞም በካህናቱ፣ በሌዋውያኑ፣ በመዘምራኑ፣ በበር ጠባቂዎቹ፣ በቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ወይም በሌሎቹ በዚህ በእግዚአብሔር ቤት ሠራተኞች ላይ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻ ለመጣል ሥልጣን እንደ ሌላችሁ ይህን ዕወቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 7