ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 5:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐጌና የአዶ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁድ ከእነርሱ በላይ በሆነው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው።

2. ከዚያም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራት ተነሡ፤ የሚያግዟቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት አብረዋቸው ነበሩ።

3. በዚህ ጊዜ በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሄደው፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ውቅሩንም ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።

4. ደግሞም፣ “ይህን ሕንጻ የሚገነቡት ሰዎች ስም ማን ይባላል?” በማለት ጠየቋቸው።

5. የአምላካቸው ዐይን ግን በአይሁድ መሪዎች ላይ ነበረ፤ ነገሩ ወደ ዳርዮስ ደርሶ የጽሑፍ መልስ እስኪያገኙ ድረስ አልተከለከሉም።

6. በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይ፣ ተባባሪዎቻቸውና በኤፍራጥስ ማዶ የነበሩ ሹማምት ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

7. የላኩትም ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤ለንጉሥ ዳርዮስ፣የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።

8. የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደን እንደ ነበር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በታላላቅ ድንጋዮች እየገነቡና ቅጥሩንም በወፍራም ምሰሶዎች እየሠሩ ነው፤ ሥራው በትጋት በመከናወንና በእነርሱም አመራር በመፋጠን ላይ ይገኛል።

9. እኛም መሪዎቹን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ይህንም ውቅር ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ብለን ጠየቅናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 5