ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለዳርዮስ የተላከ የተንትናይ ደብዳቤ

1. በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐጌና የአዶ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁድ ከእነርሱ በላይ በሆነው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው።

2. ከዚያም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራት ተነሡ፤ የሚያግዟቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት አብረዋቸው ነበሩ።

3. በዚህ ጊዜ በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሄደው፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ውቅሩንም ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።

4. ደግሞም፣ “ይህን ሕንጻ የሚገነቡት ሰዎች ስም ማን ይባላል?” በማለት ጠየቋቸው።

5. የአምላካቸው ዐይን ግን በአይሁድ መሪዎች ላይ ነበረ፤ ነገሩ ወደ ዳርዮስ ደርሶ የጽሑፍ መልስ እስኪያገኙ ድረስ አልተከለከሉም።

6. በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይ፣ ተባባሪዎቻቸውና በኤፍራጥስ ማዶ የነበሩ ሹማምት ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

7. የላኩትም ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤ለንጉሥ ዳርዮስ፣የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።

8. የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደን እንደ ነበር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በታላላቅ ድንጋዮች እየገነቡና ቅጥሩንም በወፍራም ምሰሶዎች እየሠሩ ነው፤ ሥራው በትጋት በመከናወንና በእነርሱም አመራር በመፋጠን ላይ ይገኛል።

9. እኛም መሪዎቹን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ይህንም ውቅር ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ብለን ጠየቅናቸው።

10. የመሪዎቻቸውን ስም በጽሑፍ እናሳውቅህ ዘንድ ስማቸውን ደግሞ ጠየቅን።

11. የሰጡን መልስ ይህ ነው፤“እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁንም እንደ ገና የምንሠራው ቤተ መቅደስ፣ ከብዙ ዘመናት በፊት ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የጨረሰውን ነው።

12. ነገር ግን አባቶቻችን የሰማይን አምላክ አስቈጥተውት ስለ ነበር፣ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለከለዳዊው ናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤተ መቅደስ አፈራርሶ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ።

13. “ይሁንና ቂሮስ፣ የባቢሎን ንጉሥ በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና እንዲሠሩ ንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ ሰጠ።

14. ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አውጥቶ ባቢሎን በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ከባቢሎን ቤተ መቅደስ አስመጣ።“ከዚያም ንጉሥ ቂሮስ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ለሾመውና ሰሳብሳር ተብሎ ለሚጠራው ሰው ሰጠው፤

15. ቀጥሎም፣ ‘እነዚህን ዕቃዎች ይዘህ ሂድና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ አኑራቸው፤ የእግዚአሔር ቤት ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንደ ገና ይሠራ’ አለው።

16. ስለዚህ ይህ ሰሳብሳር መጥቶ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣለ፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እነሆ በመሠራት ላይ ነው፤ ሆኖም ገና አላለቀም።

17. “አሁንም ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም እንዲሠራ ንጉሥ ቂሮስ በርግጥ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደሆነ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ያድርግ፤ ከዚያም ንጉሡ ስለዚህ ጒዳይ የወሰነውን ይላክልን።”