ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 52:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ።

5. ከተማዪቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዘመነ መንግሥት ተከባ ነበር።

6. በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን አጣ፤

7. የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።

8. የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት።

9. እርሱም በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ ተወሰደ፤ የባቢሎን ንጉሥ በዚያ ፈረደበት።

10. በሪብላም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በአባታቸው ፊት ዐረዳቸው፤ የይሁዳንም ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ገደላቸው፤

11. የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ በናስ ሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ በዚያም እስከ ዕለተ ሞቱ በእስር ቤት አቈየው።

12. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር፤ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

13. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የንጉሡን ቤተ መንግሥት እንዲሁም በኢየሩሳሌም የነበሩትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ ሌሎች ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ።

14. በክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ሰራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር በሙሉ አፈረሱ።

15. የዘቦቹ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ፣ የእጅ ጥበብ ያላቸውንና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው።

16. ነገር ግን የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።

17. ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ገንዳ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ይዘው ሄዱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 52