ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50
  51. 51
  52. 52

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 52 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኢየሩሳሌም መውደቅ

1. ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም አሚጣል ሲሆን፣ እርሷም የሊብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

2. ሴዴቅያስም ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

3. እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ይህን ሁሉ ያደረሰውንና በመጨረሻም ከፊቱ ያስወገዳቸው ከቍጣው የተነሣ ነበር።ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

4. ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ።

5. ከተማዪቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዘመነ መንግሥት ተከባ ነበር።

6. በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን አጣ፤

7. የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።

8. የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት።

9. እርሱም በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ ተወሰደ፤ የባቢሎን ንጉሥ በዚያ ፈረደበት።

10. በሪብላም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በአባታቸው ፊት ዐረዳቸው፤ የይሁዳንም ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ገደላቸው፤

11. የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ በናስ ሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ በዚያም እስከ ዕለተ ሞቱ በእስር ቤት አቈየው።

12. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር፤ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

13. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የንጉሡን ቤተ መንግሥት እንዲሁም በኢየሩሳሌም የነበሩትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ ሌሎች ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ።

14. በክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ሰራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር በሙሉ አፈረሱ።

15. የዘቦቹ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ፣ የእጅ ጥበብ ያላቸውንና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው።

16. ነገር ግን የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።

17. ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ገንዳ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ይዘው ሄዱ።

18. ከእነዚህም ሌላ ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ወጭቶችን፣ ጭልፋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የናስ ዕቃዎች በሙሉ ወሰዱ።

19. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ከንጹሕ ወርቅና ከንጹሕ ብር የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ጐድጓዳ ሳሕኖችን ጥናዎችን፣ ወጭቶችን፣ ምንቸቶችን፣ መቅረዞችን፣ ጭልፋዎችንና ለመጠጥ ቍርባን ማቅረቢያ የሚሆኑ ወጭቶችን ይዞ ሄደ።

20. ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ሚዛን ከሚችለው በላይ ነበር።

21. እያንዳንዱም ዐምድ ከፍ ታውዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለ ሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ።

22. በአንዱ ዐምድ ዐናት ላይ ያለው የናስ ጒልላት ቁመት አምስት ክንድ ሲሆን፣ ዙሪያውንም ሁሉ የሮማን ቅርጽ ባላቸው የናስ ጌጣጌጦች የተዋበ ነበር፤ ሌላውም ዐምድ የሮማኑን ጌጣጌጥ ጨምሮ ከዚሁ ጋር አንድ ዐይነት ነበር።

23. ዘጠና ስድስቱ ሮማኖች ከጐን በቀላሉ የሚታዩ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ በዙሪያው ካለው ጌጥ በላይ ያለው የሮማኖች ቍጥር አንድ መቶ ነበር።

24. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ የካህናት አለቃ የነበረውን ሠራያን፣ ምክትሉንም ካህን ሶፎንያስንና ሦስቱን በር ጠባቂዎች አስሮ ወሰዳቸው፤

25. በከተማው ውስጥ ከቀሩትም ሕዝብ፣ የተዋጊዎቹ ኀላፊ የነበረውን መኰንን፣ ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች ከአገሬው ሕዝብ ወታደር የሚመለምለውን መኰንን ጸሓፊና በከተማው ውስጥ የተገኙትን ሌሎች ስድሳ ሰዎች ወሰደ።

26. የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው።

27. ንጉሡም በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ፈጃቸው።ይሁዳም በዚህ ሁኔታ ከምድሯ በምርኮ ተወሰደች።

28. ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰደው ሕዝብ ቍጥር እንደሚከተለው ነው፦በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ሦስት ሺህ ሃያ ሦስት አይሁድ፤

29. ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራስምንተኛው ዓመት፣ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፤

30. ናቡከደነፆር በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳንሰባት መቶ አርባ አምስት አይሁድ ማርኮ ወስዶአል፤በአጠቃላይ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ነበሩ።

የዮአኪን መፈታት

31. የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ ዮርማሮዴክ በባቢሎን ነገሠ፤ በዚሁ ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ አምስተኛው ቀን የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን አሰበው፤ ከእስር ቤትም አወጣው፤

32. በመልካምም ቃል አናገረው፤ ከእርሱም ጋር በባቢሎን በምርኮ ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ባለ የክብር ቦታ አስቀመጠው።

33. ዮአኪንም እስር ቤት ለብሶት የነበረውን ልብሱን አውልቆ ጣለ፤ በቀረውም የሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከንጉሡ ማእድ ይበላ ነበር።

34. የባቢሎንም ንጉሥ፣ ዮአኪን እስኪሞት ድረስ፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ በየዕለቱ ቀለቡን ይሰጠው ነበር።