ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 49:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ስለ አሞናውያን፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እስራኤል ወንዶች ልጆች አልወለደምን?ወራሾችስ የሉትምን?ታዲያ፣ ሚልኮምሸ ጋድን ለምን ወረሰ?የእርሱ ሰዎች ለምን በከተሞቿ ይኖራሉ?

2. ስለዚህ በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ፣የጦርነት ውካታ ድምፅ፣የሚሰማበት ጊዜ ይመጣል፤”ይላል እግዚአብሔር፤“እርሷም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤በዙሪያዋ ያሉት መንደሮችም ይቃጠላሉ፤እስራኤልም ከአገሯ ያስወጧትን፣ከአገሯ ታስወጣለች፤”ይላል እግዚአብሔር፤

3. ሐሴቦን ሆይ፤ ጋይ ጠፍታለችና ዋይ በይ፤የራባት ሴቶች ልጆች ሆይ ጩኹ፤ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤ሚልኮም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋር፣ተማርኮ ይወሰዳልና፣በቅጥር ውስጥ ወዲያ ወዲህ ተሯሯጡ።

4. አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፣በሸለቆችሽ ለምን ትመኪያለሽ?ለምንስ በፍሬያማ ሸለቆሽ ትኵራሪያለሽ?በብልጽግናሽ ተማምነሽ፣‘ማን ሊነካኝ ይችላል?’ ትያለሽ።

5. በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ፣ሽብር አመጣብሻለሁ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤“እያንዳንዳችሁ ትሰደዳላችሁ፤በሽሽት ላይ ያሉትንም የሚሰበስብ አይገኝም።

6. “ከዚያ በኋላ ግን፣ የአሞናውያንን ምርኮ እመልሳለሁ፣”ይላል እግዚአብሔር።

7. ስለ ኤዶም፤የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ጥበብ ከቴማን ጠፍቶአልን?ምክር ከአስተዋዮች ርቆአልን?ጥበባቸውስ ተሟጧልን?

8. ዔሳውን በምቀጣ ጊዜ፣ጥፋት ስለማመጣበት፣እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ፤ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ሽሹ፤ ጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ተደበቁ።

9. ወይን ለቃሚዎች ወዳንተ ቢመጡ፣ጥቂት ወይን አያስቀሩምን?ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፣የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ብቻ አይደለምን?

10. እኔ ግን ዔሳውን አራቍተዋለሁ፤መደበቅም እንዳይችል፣መሸሸጊያ ስፍራዎቹን እገልጣለሁ፤ልጆቹ፣ ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ ይጠፋሉ፤እርሱም ራሱ አይኖርም።

11. ወላጆች የሌላቸውን ልጆችህን ተዋቸው፤ እኔ ለሕይወታቸው እጠነቀቃለሁ፤ መበለቶቻችሁም በእኔ ይታመኑ።”

12. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከጽዋው መጠጣት የማይገባቸው ሊጠጡ ግድ ከሆነ፣ አንተ እንዴት ሳትቀጣ ትቀራለህ? መቀጣትህ አይቀርም፤ መጠጣት ይገባሃል።

13. ባሶራ ፈራርሳ የድንጋጤ፣ የመዘባበቻና የርግማን ምልክት እንደምትሆን በራሴ ምያለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከተሞቿም ሁሉ ለዘላለም ባድማ ይሆናሉ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 49