ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 41:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እስማኤል በምጽጳ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ምርኮኛ አደረገ፤ እነርሱም የባቢሎን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡረዘረዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው ገዥ አድርጎ የሾመባቸው የንጉሡ ሴቶች ልጆችና በዚያ የቀሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የናታንያ ልጅ እስማኤል እነዚህን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ተነሣ።

11. የቃሬያ ልጅ ዮሐናና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የፈጸመውን ግፍ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣

12. የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሊወጉ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው በታላቁ ኵሬ አጠገብ ደረሱበት።

13. እስማኤል የያዛቸው ሰዎች ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና አብረውት የነበሩትን የጦር መኰንኖች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።

14. እስማኤል ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ሁሉ አምልጠው ወደ ቃሬያ ልጅ ወደ ዮሐናን ገቡ።

15. የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን አብረውት ከነበሩት ስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ፤ ሸሽቶም ወደ አሞናውያን ገባ።

16. የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ፣ በምጽጳ ከማረካቸው የተረፉትን ሰዎች በማስመለስ ይዘው ሄዱ፤ እነዚህም፦ ወታደሮች፣ ሴቶች ሕፃናትና ከገባዖን ያመጧቸው የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች ነበሩ።

17. ከዚያም ተነሥተው ሄዱ፤ ወደ ግብፅም በማምራት በቤተልሔም አጠገብ ባለችው በጌሮት ከመዓም ዐረፉ፤

18. ወደ ግብፅም የሄዱት ከባቢሎናውያን ለማምለጥ ነበር፤ ባቢሎናውያንንም የፈሩት የናታንያ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ የምድሪቱ ገዥ አድርጎ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመግደሉ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 41