ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50
  51. 51
  52. 52

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 41 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የሆነው ከንጉሡ የጦር መኰንንኖች አንዱ የነበረው የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ በሰባተኛው ወር ከዐሥር ሰዎች ጋር ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፣ በዚያም በአንድነት ሊበሉ በማእድ ተቀምጠው ሳለ፣

2. የናታንያ ልጅ እስማኤልና አብረውት የነበሩ ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው፣ የባቢሎን ንጉሥ በምድሪቱ ላይ ገዥ አድርጎ የሾመውን የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱት፤ ገደሉትም።

3. ደግሞም እስማኤል በምጽጳ ከጎዶልያስ ጋር የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፣ በዚያም የተገኙትን የባቢሎን ወታደሮች ገደላቸው።

4. ጎዶልያስ በተገደለ ማግስት፣ ማንም ስለ ሁኔታው ከማወቁ በፊት፣

5. ሰማንያ ሰዎች ጢማቸውን ተላጭተው፣ ልበሳቸውን ቀደው፣ ገላቸውን ነጭተው የእህል ቍርባንና ዕጣን በመያዝ ከሴኬም፣ ከሴሎና ከሰማርያ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማቅረብ መጡ።

6. የናታንያ ልጅ እስማኤል ሊገናኛቸው እያለቀሰ ከምጽጳ ወጣ፣ ሲያገኛቸውም፣ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑቃ አላቸው።

7. ወደ ከተማዪቱ በገቡ ጊዜ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤልና አብረውት የነበሩ ሰዎች ዐረዷቸው፤ በውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ውስጥም ጣሏቸው።

8. ከተገደሉት ጋር የነበሩ ዐሥር ሰዎች ግን እስማኤልን፣ “እባክህ አትግደለን! በዕርሻችን ውስጥ የሸሸግነው ስንዴና ገብስ፣ የወይራ ዘይትና ማር ስላለን እባክህን አትግደለን” አሉት። እርሱም ተዋቸው፤ ከሌሎቹም ጋር አልገደላቸውም።

9. እስማኤል ከጎዶልያስ በተጨማሪ የገደላቸው ሰዎች ሁሉ ሬሳ የተጣለበት የውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ ለመከላከል ያሠራው ነበር፤ ይህን ጒድጓድ፤ የናታንያ ልጅ እስማኤል በሬሳ ሞላው።

10. እስማኤል በምጽጳ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ምርኮኛ አደረገ፤ እነርሱም የባቢሎን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡረዘረዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው ገዥ አድርጎ የሾመባቸው የንጉሡ ሴቶች ልጆችና በዚያ የቀሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የናታንያ ልጅ እስማኤል እነዚህን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ተነሣ።

11. የቃሬያ ልጅ ዮሐናና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የፈጸመውን ግፍ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣

12. የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሊወጉ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው በታላቁ ኵሬ አጠገብ ደረሱበት።

13. እስማኤል የያዛቸው ሰዎች ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና አብረውት የነበሩትን የጦር መኰንኖች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።

14. እስማኤል ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ሁሉ አምልጠው ወደ ቃሬያ ልጅ ወደ ዮሐናን ገቡ።

15. የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን አብረውት ከነበሩት ስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ፤ ሸሽቶም ወደ አሞናውያን ገባ።

ሽሽት ወደ ግብፅ

16. የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ፣ በምጽጳ ከማረካቸው የተረፉትን ሰዎች በማስመለስ ይዘው ሄዱ፤ እነዚህም፦ ወታደሮች፣ ሴቶች ሕፃናትና ከገባዖን ያመጧቸው የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች ነበሩ።

17. ከዚያም ተነሥተው ሄዱ፤ ወደ ግብፅም በማምራት በቤተልሔም አጠገብ ባለችው በጌሮት ከመዓም ዐረፉ፤

18. ወደ ግብፅም የሄዱት ከባቢሎናውያን ለማምለጥ ነበር፤ ባቢሎናውያንንም የፈሩት የናታንያ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ የምድሪቱ ገዥ አድርጎ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመግደሉ ነው።