ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 38:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኤርምያስ ለሕዝቡ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ሰፋጥያስ፣ የጳስኮር ልጅ ጎዶልያስ፣ የሰሌምያ ልጅ ዮካል እንዲሁም የመልክያ ልጅ ጳስኮር ሰሙ፤ ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦

2. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህች ከተማ የሚቀር ሁሉ በሰይፍ፣ በራብ ወይም በቸነፈር ይሞታል፤ ይህን ስፍራ ለቆ ወደ ባቢሎናውያን የሚሄድ ሁሉ ይተርፋል፤ ያመልጣል፤ በሕይወትም ይኖራል።’

3. እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፤ ‘ይህች ከተማ በእርግጥ ለባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ዐልፋ ትሰጣለች፤ እርሱም ይይዛታል።’ ”

4. መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው በሚናገረው ነገር በዚህች ከተማ የቀሩትን ወታደሮችና ሕዝቡንም ሁሉ ተስፋ የሚያስቈርጥ ስለ ሆነ መሞት አለበት፤ ይህ ሰው የሕዝቡን መጥፋት እንጂ መልካም ነገር አይሻም።”

5. ንጉሡ ሴዴቅያስም፤ “እርሱ በእጃችሁ ነው፤ ንጉሡ እናንተን ተቃውሞ ምንም ማድረግ አይችልም” አለ።

6. ስለዚህ ኤርምያስን ወስደው፣ በዘበኞች አደባባይ በነበረው በንጉሡ ልጅ በመልክያ የውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በገመድም ኤርምያስን ወደ ጒድጓዱ አወረዱት። ጒድጓዱም ጭቃ እንጂ ውሃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ዘልቆ ገባ።

7. በቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አቤሜሌክ፣ ኤርምያስን በውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ውስጥ እንደ ጣሉት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ሳለ፣

8. አቤሜሌክ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፤

9. “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች በነቢዩ በኤርምያስ ላይ ባደረጉት ነገር ሁሉ ክፋትን አድርገዋል፤ ከከተማዪቱም እንጀራ በጠፋ ጊዜ በራብ እንዲሞት ጒድጓድ ውስጥ ጥለውታል።”

10. ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፣ “ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ይዘህ ሂድ፤ ነቢዩ ኤርምያስንም ሳይሞት ከጒድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው።

11. አቤሜሌክም ሰዎቹን ይዞ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ሥር ወዳለው ክፍል ሄደ፤ ያረጀ ጨርቅና ያለቀ ልብስ ከዚያ ወስዶ ወደ ኤርምያስ ወደ ጒድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደለት።

12. ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን፣ “ይህን ያረጀ ጨርቅና ያረጀ ልብስ ገመዱ እንዳይከረክርህ በብብትህ ሥር አድርገው አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ፤

13. እነርሱም በገመዱ ጐትተው ከጒድጓዱ አወጡት። ኤርምያስም በዘበኞች አደባባይ ሰነበተ።

14. ንጉሡ ሴዴቅያስ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ልኮ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሦስተኛው በር አስመጣውና፤ “አንድ ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 38