ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 20:2-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ነቢዩ ኤርምያስን መታው፣ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በላይኛው የብንያም በር በእግር ግንድ ጠረቀው።

3. በማግስቱም ጳስኮር ኤርምያስን ከተጠረቀበት ግንድ አወጣው፤ ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ከእንግዲህ ማጎርሚሳቢብ ብሎ ይጠራሃል እንጂ ጳስኮር አይልህም፤

4. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘አንተንና ባልንጀሮችህን ሁሉ ለሽብር እዳርጋለሁ፤ የገዛ ዐይንህ እያየ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። ይሁዳን ሁሉ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል።

5. የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ፣ ጥሪቷን፣ የይሁዳን ነገሥታት ውድ ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ዘርፈው ወደ ባቢሎን ይዘውት ይሄዳሉ።

6. ጳስኮር ሆይ፤ አንተና በቤትህ የሚኖሩት ሁሉ ወደ ባቢሎን ትጋዛላችሁ። አንተና በሐሰት ትንቢት የተነበይህላቸው ባልንጆሮችህ በዚያ ትሞታላችሁ፤ በዚያም ትቀበራላችሁ።’ ”

7. እግዚአብሔር ሆይ፤ አታለልኸኝ፤ እኔም ተታለልሁ፤አንተ ከእኔ እጅግ በረታህ፤ አሸነፍህም፤ቀኑን ሙሉ ማላገጫ ሆንሁ፤ሁሉም ተዘባበቱብኝ።

8. በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤“ሁከትና ጥፋት!” ብዬ ዐውጃለሁ፤ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል፣ቀኑን ሙሉ ስድብና ነቀፋ አስከተለብኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 20