ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 9:5-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ሰዎቹም ያረጀና የተጠጋገነ ነጠላ ጫማ አድርገዋል፤ አሮጌ ልብስ ለብሰዋል፤ ለስንቅ የያዙት እንጀራም በሙሉ የደረቀና የሻገተ ነበር።

6. ከዚያም ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ኢያሱንና የእስራኤልን ሰዎች፣ “የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ” አሏቸው።

7. የእስራኤልም ሰዎች ለኤዊያውያኑ፣ “እናንተ የምትኖሩት እዚሁ ቅርብ ቢሆንስ? ታዲያ ከእናንተ ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንገባለን?” አሏቸው።

8. እነርሱም ኢያሱን፣ “እኛ ባሪያዎችህ ነን” አሉት።ኢያሱ ግን፣ “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

9. እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “እኛ ባሪያዎችህ የአምላካህን የእግዚአብሔርን ዝና ሰምተን፣ እጅግ ሩቅ ከሆነ አገር መጥተናል፤ ዝናውንና በግብፅ ያደረገውንም ሁሉ ሰምተናል፤

10. እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ ባሉት በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለትም በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን፣ አስታሮትን ይገዛ በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ነው።

11. ሽማግሌዎቻችንና በአገራችን የሚኖሩት ሁሉ፣ ‘ለመንገዳችሁ የሚሆን ስንቅ ያዙ፤ ሄዳችሁም ተገናኟቸው፤ እኛ ባሮቻችሁ እንሆናለን፤ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግቡ በሉአቸው’ አሉን።

12. ይህ የያዝነው እንጀራ ወደ እናንተ ለመምጣት ከቤታችን በተነሣንበት ቀን ትኵስ ነበር፤ አሁን ግን እንዴት እንደ ደረቀና እንደሻገተ ተመልከቱ።

13. እነዚህ የወይን ጠጅ አቍማዳዎቻችን ያን ጊዜ ስንሞላቸው አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን እንዴት እንደተ ቀዳደዱ ተመልከቱ፤ ልብሳችንና ጫማችንም ብዙ መንገድ በመጓዛችን አልቀዋል።”

14. የእስራኤልም ሰዎች ከስንቃችው ላይ ጥቂት ወሰዱ፤ ስለ ጒዳዩ ግን እግዚአብሔርን አልጠየቁም ነበር።

15. ኢያሱም በሰላም ለመኖር የሚያስችላቸውን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ የጉባኤውም መሪዎች ይህንኑ በመሓላ አጸኑላቸው።

16. እስራኤላውያን ከገባዖን ሰዎች ጋር ቃል ኪዳኑን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ፣ ሰዎቹ እዚያው አጠገባቸው የሚኖሩ ጎረቤቶቻቸው መሆናቸውን ሰሙ።

17. ስለዚህ እስራኤላውያን ተጒዘው በሦስተኛው ቀን ገባዖን፣ ከፊራ፣ ብኤሮትና ቂርያትይዓይሪም ወደተባሉት የገባዖን ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ከተሞች መጡ።

18. ሆኖም እስራኤላውያን አልወጓቸውም፤ የጉባዔው መሪዎች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ምለውላቸው ነበርና።ማኅበሩም ሁሉ በመሪዎቹ ላይ አጒረመረሙ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 9