ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ ከእስራኤላውያንም ሁሉ ጋር ከሰጢም ወደ ዮርዳኖስ መጥተው፣ ወንዙን ከመሻገራቸው በፊት በዚያ ሰፈሩ።

2. ከሦስት ቀን በኋላም የጦሩ አለቆች በሰፈር ውስጥ አለፉ፤

3. ሕዝቡንም እንዲህ ሲሉ አዘዙ፤ “ሌዋውያን ካህናቱ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ፣ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ታቦቱን ተከተሉ፤

4. ካሁን በፊት በዚህ መንገድ ሄዳችሁ ስለማታውቁ፤ በየት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ፤ ሆኖም በታቦቱና በእናንተ መካከል የሁለት ሺህ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱም አትቅረቡ።”

5. ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን፣ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በመካከላችሁ አስደናቂ ነገር ስለሚያደርግ ራሳችሁን ቀድሱ” አላቸው።

6. ኢያሱም ካህናቱን፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ ሕዝቡን ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ታቦቱን ተሸክመው ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ።

7. እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ፣ በእስራኤል ሁሉ ፊት አንተን ከፍ ከፍ ማድረጌን በዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ።

8. የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትንም ካህናት፣ ‘ከዮርዳኖስ ውሃ ዳር ስትደርሱ፣ በወንዙ ውስጥ ገብታችሁ ቁሙ’ በላቸው።”

9. ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ “ወደዚህ ቀርባችሁ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አላቸው፤

10. እንግዲህ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ መሆኑንና እርሱም በእርግጥ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ኤዊያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ እንዴት አድርጎ እንደሚያሳድዳቸው የምታውቁት በዚህ ነው።

11. እነሆ፤ የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት ቀድሞአችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል።

12. እንግዲህ ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰው ምረጡ፤ ከየነገዱም አንዳንድ ሰው ይሁን።

13. የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ገና እግራቸውን በዮርዳኖስ ውሃ ውስጥ እንዳስ ገቡ፣ ቊልቊል የሚወርደው ውሃ ወዲያውኑ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።”

14. ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ሰፈሩን ለቀው ሲወጡ፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከፊታቸው ቀድመው ሄዱ።

15. ወቅቱም የመከር ጊዜ በመሆኑ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ነበር፤ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 3