ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 11:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የአሦር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ ማዶን ንጉሥ፣ ወደ ዮባብ ንጉሥ፣ ወደ ሺምሮን ንጉሥ፣ ወደ አዚፍ ንጉሥ ላከ፤

2. እንዲሁም በተራራማው አገር ከኪኔሬት ደቡብ በዓረባ፣ በምዕራቡ ቈላ አገርና ከዶር ኰረብታ በስተ ምዕራብ ወዳሉት ነገሥታት ላከ፤

3. ደግሞም በምሥራቅና በምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያንና በኰረብታማው አገር ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን፣ እንዲሁም ደግሞ በምጽጳ ምድር በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ወዳሉት ወደ ኤዊያውያን ነገሥታት መልእክት ላከ።

4. እነዚህም ሰራዊታቸውን ሁሉ እጅግ ብዙ ከሆኑ ፈረሶችና ሠረገሎች ጋር ይዘው ወጡ፤ የሰራዊቱም ብዛት በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበር።

5. እነዚህ ሁሉ ነገሥታት እስራኤልን ለመውጋት ኀይላቸውን አስተባብረው በማሮን ውሃ አጠገብ በአንድነት ሰፈሩ።

6. እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነዚህን ሁሉ ነገ በዚች ሰዓት እንደ ሙት አድርጌ፣ በእስራኤል እጅ አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም ታቃጥላለህ” አለው።

7. ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ ሁሉ በድንገት ወደ ማሮን ውሃ መጥተው ወጓቸው።

8. እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ስለሰጣቸው ድል አደረጓቸው፤ በታላቂቱ ሲዶና መንገድ መጨረሻ እስከ ማስሮን፣ በስተ ምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዷቸው፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 11