ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 59:5-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. የእባብ ዕንቍላል ታቀፉ፤የሸረሪት ድር አደሩ፤ዕንቍላሎቻቸውን የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤አንዱ በተሰበረ ጊዜም እፉኝት ይወጣል።

6. ድሮቻቸው ልብስ አይሆኑም፤በሚሠሩትም ሰውነታቸውን መሸፈን አይችሉም፤ሥራቸው ክፉ ነው፤እጃቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞላ ነው።

7. እግሮቻቸው ወደ ኀጢአት ይሮጣሉ፤ንጹሕ ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤የሚያስቡት ክፉ ሐሳብ ነው፤ማጥፋትና ማፈራረስም የመንገዳቸው ምልክት ነው።

8. የሰላምን መንገድ አያውቁም፤በጐዳናቸውም ፍትሕ የለም፤መንገዳቸውን ጠማማ አድርገውታል፤በዚያም የሚሄድ ሰላም አያገኝም።

9. ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቆአል፤ጽድቅም ወደ እኛ አይመጣም፤ብርሃንን ፈለግን፤ ነገር ግን ሁሉ ጨለማ ነው፤የብርሃንን ጸዳል ፈለግን፤ የምንሄደው ግን በድንግዝግዝታ ነው።

10. በቅጥሩ ላይ እንደ ዕውር ተደናበርን፤አካሄዳችንም ዐይን እንደሌላቸው በዳበሳ ሆነ፤ጀምበር በምትጠልቅበት ጊዜ እንደሚሆነው በእኩለ ቀን ተደናበርን፤በብርቱዎች መካከልም እንደ ሙታን ሆንን።

11. ሁላችን እንደ ድቦች እናላዝናለን፤እንደ ርግቦችም በመቃተት እንጮኻለን፤ፍትሕን ፈለግን፤ ግን አላገኘንም፤ትድግናን ፈለግን፤ ነገር ግን ከእኛ ርቆአል።

12. በደላችን በፊትህ በዝቶአል፤ኀጢአታችን መስክሮብናል፤በደላችን ከእኛ አልተለየም፤ዐመፀኝነታችንንም እናውቃለን።

13. በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ሐሰት ተናግረናል፤አምላካችንን ከመከተል ዘወር ብለናል፤ዐመፃንና ግፍን አውርተናል፤ልባችን የፀነሰውን ውሸት ተናግረናል።

14. ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቆአል፤ጽድቅም በሩቁ ቆሞአል፤እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሎአል፤ቅንነትም መግባት አልቻለም።

15. እውነት የትም ቦታ አይገኝም፤ከክፋት የሚርቅ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። እግዚአብሔር ተመለከተ፤ፍትሕ በመታጣቱም ዐዘነ።

16. ማንም እንደሌለ አየ፤ወደ እርሱ የሚማልድ ባለመኖሩ ተገረመ፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ ድነት አመጣለት፤የራሱም ጽድቅ ደግፎ ያዘው።

17. ጽድቅን እንደ ጥሩር አጠለቀ፤የድነትን ቊር በራሱ ላይ ደፋ፤የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤መጐናጸፊያ እንደሚደረብም ቅናትን ደረበ።

18. እንደ ሥራቸው መጠን፣ቊጣን ለባላጋራዎቹ፣ፍዳን ለጠላቶቹ፣እንደዚሁ ይከፍላቸዋል፤ለደሴቶችም የእጃቸውን ይሰጣቸዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 59