ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 57:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ከመዝጊያሽና ከመቃንሽ ጀርባ፣የጣዖት ምስሎችሽን ሰቀልሽ፤እኔን ትተሽ መኝታሽን ገላለጥሽ፤በላይም ወጥተሽ በጣም ገለጥሽው፤መኝታቸውን ከወደድሽላቸው ጋር ስምምነት አደረግሽ፤ዕርቃናቸውንም አየሽ።

9. የወይራ ዘይት ይዘሽ፣ሽቶ በላዩ ጨምረሽ ወደ ሞሎክ ሄድሽ፤መልእክተኞችሽን ወደ ሩቅ አገር ላክሽ፤እስከ ራሱ እስከ ሲኦልም ዘለቅሽ።

10. በመንገድ ብዛት ደከምሽ፤ነገር ግን ‘ተስፋ የለውም’ አላልሽም፤የጒልበት መታደስ አገኘሽ፤ስለዚህም አልዛልሽም።

11. “እኔን የዋሸሽኝ፤ማንን ፈርተሽ፣ ማንንስ ሠግተሽ ነው?እኔን ያላስታወስሽው፣ይህንንም በልብሽ ያላኖርሽው፣እኔን ያልፈራሽው፣ዝም ስላልሁ አይደለምን?

12. ጽድቅሽንና ሥራሽን አጋልጣለሁ፤እነርሱም አይጠቅሙሽም።

13. ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስቲ ያድኑሽ!ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ሽውሽውታም ይበትናቸዋል።እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ምድሪቱን ይወርሳል፤የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”

14. እንዲህ ይባላል፤“አብጁ፤ አብጁ፤ መንገድ አዘጋጁ፤ከሕዝቤ መንገድ ዕንቅፋት አስወግዱ።”

15. ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤“የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።

16. የሰው መንፈስ በፊቴ እንዳይዝል፣የፈጠርሁትም ሰው እስትንፋስ እንዳይቆም፣ለዘላለም አልወቅስም፤ሁልጊዜም አልቈጣም።

17. ኀጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቍጣ ከእርሱ ሸሸግሁ፤ያም ሆኖ በገዛ መንገዱ ገፋበት።

18. መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትምመጽናናትን እመልሳለሁ፤

19. በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምስጋና እፈጥራለሁ።በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤እኔ እፈውሳቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

20. ክፉዎች ግን ማዕበሉ ጭቃና ጒድፍ እንደሚያወጣ፣ጸጥ ማለት እንደማይችል፣እንደሚናወጥ ባሕር ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 57