ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 51:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. የዳኑት እንዲሻገሩ ባሕሩን፣የታላቁን ጥልቅ ውሆች ያደረቅህ፣በጥልቁም ውስጥ መንገድ ያበጀህ፣አንተ አይደለህምን?

11. እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤የዘላለማዊ ደስታን አክሊል ይቀዳጃሉ፤ተድላና ደስታ ያገኛሉ፤ሐዘንና ልቅሶም ከእነርሱ ይሸሻል።

12. “የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤ሟች የሆኑትን ሰዎች፣እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆችለምን ትፈራለህ?

13. የፈጠረህን፣ሰማያትን የዘረጋውን፣ምድርን የመሠረተውን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤ሊያጠፋህ ከተዘጋጀው፣ከጨቋኙ ቊጣ የተነሣ፣በየቀኑ በሽብር ትኖራለህ፤ታዲያ የጨቋኙ ቊጣ የት አለ?

14. ዐንገታቸውን የደፉ እስረኞች በፍጥነት ነጻ ይወጣሉ፤በታሰሩበትም ጒድጓድ ውስጥ አይሞቱም፤እንጀራ አያጡም።

15. ሞገዱ እንዲተም ባሕሩን የማናውጥ፣እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

16. ቃሌን በአፍህ አኖርሁ፤በእጄ ጥላ ጋረድሁህ፤ሰማያትን በስፍራቸው ያስቀመጥሁ፣ምድርን የመሠረትሁ፣ጽዮንንም፣ ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’ ያልሁ እኔ ነኝ።

17. ከእግዚአብሔር እጅ፣የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ፣ዝቃጩ እንኳ ሳይቀር፣ሰዎችን የሚያንገደግደውን ዋንጫ የጨለጥሽ፣ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤ተነሺ፤ ተነሺ።

18. ከወለደቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ፣የመራት አንድም አልነበረም፤ካሳደገቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ፣እጇን ይዞ የወሰዳት ማንም አልነበረም።

19. እነሆ፤ በጥፋት ላይ ጥፋት መጥተውብሻል፤ታዲያ ማን ያጽናናሻል?እነርሱም መፈራረስና ጥፋት፣ ራብና ሰይፍ ናቸው፤ታዲያ ማን ያስተዛዝንሽኀሀ

20. ወንዶች ልጆችሽ ዝለዋል፤በወጥመድ እንደ ተያዘ ሚዳቋ፣በየጐዳናው አደባባይ ላይ ተኝተዋል። የእግዚአብሔር ቊጣ፣የአምላክሽም ተግሣጽ ሞልቶባቸዋል።

21. ስለዚህ አንቺ የተጐዳሽ፣ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ ይህን ስሚ።

22. ሕዝቡን የሚታደግ አምላክሽ፣ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ ከእጅሽ፣ያንገደገደሽን ጽዋ ወስጃለሁ፤ያንን ጽዋ፣ የቊጣዬን ዋንጫ፣ዳግም አትጠጪውም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 51